ምስጢረ ሥላሴ

«መቅድመ ኩሉ ንሰብክ ሥላሴ ዕሩየ ወቅዱስ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ከሁሉ አስቀድመን በአካል ልዩ በቅድስና (በክብር) አንድ የሆነውን ሦስትነት እንሰብካለን። ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው» ሲል ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) አስተምሮአል (ሃይማኖተ አበው፣ጎርጎርዮስ፣ ገጽ ፪፻፲)።
የምስጢረ ሥላሴ መሠረቱና ምንጩ ቅዱስ መጽሐፍ ነው። የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት በሚገባ ጐልቶ የተገለጸው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባለመለወጥ ፍጹም ስው ከሆነ ወዲህ ነው።
በመለኮት፣ በባህርይ (በህላዌ)፣ በፈቃድና በሥልጣን አንድ የሆነው እግዚአብሔር፣ የአካል፣ የገጽ፣ የስምና የግብር ሦስትነት እንዳለው የምናምነው እምነት ምስጢረ ሥላሴ ይባላል። በመለኮት አንድ የሆነው እግዚአብሔር፣ የአካል ሦስትነት አለው ማለት፣ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ይባላል ማለት ነው። በሌላም አነጋገር፣ ለአብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ ለወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ እንዳለው የምናምነው እምነት ምስጢረ ሥላሴ ይባላል። የሦስቱም (የሥላሴም) የስም ሦስትነት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ነው። የግብር ሦስትነታቸውም አብ ወላዲ ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ነው። ይኸውም፣ ወላዲነት፣ ተወላዲነት፣ ሠራፂነት ማለት ነው።




